ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፴፰


ክፍል ፻፴፰

በጥቅምት ፫፣ ፲፱፻፲፰ (እ.አ.አ.) በሶልት ሌክ ስቲ፣ ዩታ ውስጥ ለፕሬዘደንት ጆሴፍ ኤፍ ስሚዝ የተሰጠ ራዕይ። በጥቅምት ፬፣ ፲፱፻፲፰ (እ.አ.አ.) በ፹፱ነኛው የቤተክርስቲያኗ የግማሽ አመት አጠቃላይ ጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ፣ ፕሬዘደንት ስሚዝ ባለፉት ወራት የተለያዩ መለኮታዊ መልእክቶችን እንደተቀበሉ ገለጹ። ፕሬዘደንት ስሚዝ ባለፈው ቀን ከተቀበሏቸው ከእነዚህ አንዱ አዳኝ ሰውነቱ በመቃብር ውስጥ እያለ የሙታንን መንፈስ መጎብኘቱን በሚመለከት ነበር። በጉባኤው መዝጊያ ወዲያውም ተፅፎ ነበር። በጥቅምት ፴፩፣ ፲፰፻፲፰ (እ.አ.አ.) ይህም ለቀዳሚ አመራር አማካሪዎች፣ ለአስራ ሑለቱ ቡድን፣ እና ለፔትሪያርክ ቀረበ፣ እና እነርሱም በአንድ ድምፅ ተቀብለውት ነበር።

፩–፲፣ ፕሬዘደንት ጆሴፍ ኤፍ ስሚዝ ስለ ጴጥሮስ ፅሁፎች እና ጌታ የመንፈስ አለምን ስለመጎብኘቱ ያሰላስሉ ነበር፤ ፲፩–፳፬፣ ፕሬዘደንት ስሚዝ የሞቱት ጻድቃን በገነት ውስጥ ተሰብስበው እና ክርስቶስም በመካከላቸው ያገለገለበትን አዩ፤ ፳፭–፴፯፣ በመናፍስትም መካከል ወንጌልን ለመስበክ እንዴት እንደተደራጀም ተመለከቱ፤ ፴፰–፶፪፣ ከሞት ከመነሳታቸው በፊት የመንፈስ ሁኔታቸውን እንደ ባርነት የሚመለከቱትን አዳምን፣ ሔዋንን፣ እና ብዙ ቅዱሳን ነቢያትን በመንፈስ አለም ውስጥ አዩአቸው፤ ፶፫–፷፣ ዛሬ በፅድቅ የሚሞቱ በመንፈስ አለም ውስጥ አገልግሎታቸውን ይቀጥላሉ።

በጥቅምት ሶስተኛው ቀን፣ በአስራ ዘጠኝ መቶ አስራ ስምንት አመተ ምህረት ውስጥ፣ ቅዱሳን መጻህፍትን በክፍሌ ቁጭ ብዬ አሰላስል ነበር፤

እና ለአለም ቤዛነት፣ የእግዚአብሔር ልጅ ያደረገውን ታላቅ የኃጢአት ክፍያ እያሰብኩ ነበር፤

እና የቤዛው ወደአለም መምጣት አብ እና ወልድ ያሳዩትን ታላቅ እና አስደናቂ ፍቅርም

በእርሱ የኃጢአት ክፍያ፣ እና በወንጌሉ መሰረታዊ መርሆች ታዛዥነት፣ የሰው ዘር ይድን ዘንድ እንደ ሆነ አሰላስል ነበር።

በዚህ ተይዤ እያለሁ፣ ከጌታ መሰቀል በኋላ ወንጌሉ ተሰብኮላቸው ለነበሩት በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያም፣ እና በሌሎች የእስያ ክፍሎች ውስጥ ለተበተኑት የጥንት ቅዱሳን ሐዋሪያው ጴጥሮስ ወደጻፈው አዕምሮዬ ተመለሰ።

መፅሐፍ ቅዱስን ከፈትኩ እና የጴጥሮስን የመጀመሪያ መልእክት ሶስተኛ እና አራተኛውን ምዕራፎች አነበብኩኝ፣ እና ሳነብም ቀድሞ ከነበሩት በላይ በሚቀጥሉት ምንባቦች በጣም ተነካሁ፥

“ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥

“በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤

“ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።” (፩ ጴጥሮስ ፫፥፲፰–፳)።

“እንደሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባቸው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር እንዲኖሩ ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው ነበርና።” (፩ ጴጥሮስ ፬፥፮)።

፲፩ ስለእነዚህ ስለተጻፉት ነገሮች ሳሰላስል፣ የመረዳት አይኖቼ ተከፈቱ፣ እና የጌታ መንፈስ አረፈብኝ፣ እና ታላቁንና ታናሹን የሙታን ሰራዊትን አየሁ።

፲፪ እና በዚያም በአንድ ስፍራም አብረው የተሰበሰቡ፣ በስጋ ሲኖሩ በኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ታማኝ የነበሩ፣ ቁጥራቸው ታላቅ የሆኑ የጻድቃን የመንፈስ ቡድኖች ነበሩ፤

፲፫ እና እንደ እግዚአብሔር ልጅ አይነት ታላቅ መስዋዕት ያቀረቡ፣ እና በቤዛው ስምም ስቃይንም የተቀበሉ ነበሩ።

፲፬ እነዚህ ሁሉ በአብ እግዚአብሔር እና በአንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አማካይነት ለክብሩ ትንሳኤ ፅኑ ተስፋ ኖሮአቸው ከስጋ ህይወት ተለይተው ነበር።

፲፭ በደስታ እና በተድላ ተሞልተው እንደነበሩም አየሁ፣ እና የሚድኑበት ቀን ስለመጣ አብረው ተደስተው ነበር።

፲፮ ከሞት እስራት ቤዛነታቸውን ይገለጽ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ መንፈስ አለም መምጣትን ተሰብስበው ይጠባበቁ ነበር።

፲፯ ያንቀላፋውም ትቢያ የሆነው አካላቸው ወደ ፍጹም ትክክለኛው መልክ፣ አጥንትም ከአጥንቱ፣ እና ጅማትና ስጋ በእነርሱም ላይ በዳግም እንዲመለስ፣ እና መንፈስም ከሰውነት ጋር ደግሞም እንዳይለያዩ፣ የደስታ ሙላትን ይቀበሉ ዘንድ ነበር።

፲፰ ብዙዎች ከሞት ሰንሰለት በሚድኑበት ሰአት እየተደሰቱ፣ እየጠበቁ ሲነጋገሩም፣ የእግዚአብሔር ልጅ ታማኝ ለነበሩት ለታሰሩት ነጻነትን በማወጅ መጣ፤

፲፱ እና እዛም ዘለአለማዊ ወንጌልን፣ የትንሳኤን እና የሰው ዘር ከውድቀትና ከግል ኃጢአት ንስሀ ስለመግባት የቤዛነትን ትምህርት ሰበከላቸው

ነገር ግን ለክፉዎቹ አልሄደም፣ እና እግዚአብሔርን በሚጠሉት መካከል እና በስጋ እያሉ ንስሀ ላልገቡ ራሳቸውን ወዳበላሹትም ድምጹ አለተነሳም።

፳፩ ወይም የጥንት ነቢያትን ምስክሮች እና ማስጠንቀቂያዎችን ያስወገዱት አመጸኞችም ፊቱን አላዩትም፣ ወይም ፊቱንም አልተመለከቱም።

፳፪ እነዚህም በነበሩበት ጭለማ ነገሰ፣ ነገር ግን በጻድቃን መካከል ሰላም ነበር፤

፳፫ እና ቅዱሳንም በቤዛነታቸው ተደሰቱ፣ እናም በጉልበታቸው ተንበርክከው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደቤዛቸው እና ከሞት እና ከገሀነም ሰንሰለት ያዳናቸው እንደሆነም አምነው ተቀበሉ።

፳፬ መልካቸውም በራ፣ እና የጌታ ድምቀትም በእነርሱ ላይ አረፈ፣ እና ለቅዱስ ስሙም ምስጋናን ዘመሩ

፳፭ አዳኝ በአይሁድና በእስራኤል ቤት መካከል በአገልግሎቱ፣ ዘለአለማዊ ወንጌልን ሊያስተምራቸው እንደተጋ እና ለንስሀም ለመጥራት ሶስት አመታትን እንዳሳለፈ ስለገባኝ ተደነቅሁኝም፤

፳፮ እና ግን፣ ምንም እንኳን በታላቅ ሀይል እና ስልጣን ታላቅ ስራዎች፣ እና ተዕምራትን ቢሰራም እውነትንም ቢያውጅ፣ ከጥቂቶች በስተቀር ድምጹን ያደመጡና በመገኘቱም የተደሰቱ፣ እና ከእጆቹም ደህንነትን የተቀበሉ ብዙ አልነበሩም።

፳፯ ነገር ግን ከሞቱት መካከል የነበረው አገልግሎቱ በተሰቀለበት እና በትንሳኤው መካከል በነበረው ጥቂት ጊዜ የተወሰነ ነበር፤

፳፰ ስለጴጥሮስ ቃላትም አሰብኩ—በዚህም ውስጥ እንዲህ አለ የእግዚአብሔር ልጅ ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ ላልታዘዙትም—እና ከእነርሱ ጋር በነበረው አጭር ጊዜ ለእነዚያ መንፈሶች ለመስበክ እና አስፈላጊ የሆነውን አገልግሎት ለመፈጸም እንዴት ነበር የቻለው።

፳፱ እና ስለዚህም ሳስብ፣ አይኖቼ ተከፈቱ፣ እና ተረዳሁኝም፣ እና በክፉዎች እና ታዛዥ ባልሆኑት እውነትንም በካዱት መካከል እንዲያስተምራቸው ጌታ እንዳልሄደም ታየኝ፤

ነገር ግን እነሆ፣ ከጻድቃን መካከል ሀይሎቹን አደራጀ እና ሀይል እና ስልጣንን የተላበሱ መልእክተኞቹን መደበ፣ እና እንዲሄዱና የወንጌሉን ብርሀን በጭለማ ላሉት፣ እንዲሁም ለሁሉም የሰዎች መንፈሶች እንዲወስዱ ሀላፊነትን ሰጣቸው፤ እና በዚህም ወንጌሉ ለሙታን ተሰብኮ ነበር።

፴፩ እና የተመረጡት መልእክተኞችም ጌታን የመቀበልን ቀን በማወጅ እና ለታሰሩት፣ እንዲሁም ለኃጢአታቸው ንስሀ በመግባት ወንጌሉን ለሚቀበሉት ነጻነትን በመግለጥ ሄዱ።

፴፪ እንደዚህም ነበር በኃጢአታቸው፣ እውነትን ያለማወቅ ወይም በመተላለፍ፣ ነቢያትን አስወግደው ለሞቱት ወንጌሉ የተሰበከው።

፴፫ እነዚህም በእግዚአብሔር እምነትን፣ ለኃጢአት ንስሀ መግባትን፣ ለኃጢአት ስርየት የውክልና ጥምቀትን፣ እጆችን በመጫን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ተምረው ነበር።

፴፬ እና እንደሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባቸው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ይኖሩ ዘንድ ራሳቸውን ብቁ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን የወንጌል መሰረታዊ መርሆችን ሁሉ ተምረው ነበር።

፴፭ እና ስለዚህ በታናሹና በታላቁ፣ ጻድቅ ባልሆነው እና በታማኙ፣ ቤዛነት በእግዚአብሔር ልጅ በመስቀል ላይ ባቀረበው መስዋዕት በኩል እንደመጣ በሙታኑ መካከል ታወቀ።

፴፮ እንደዚህም አዳኛችን በመንፈስ አለም በቆየበት ጊዜ በስጋቸው ስለእርሱ የመሰከሩትን ታማኝ ነቢያት መናፍስትን በማስተማር እና በማዘጋጀት ጊዜውን አንዳሳለፈ ታውቋል፤

፴፯ በአመጻቸው እና በመተላለፋቸው ምክንያት ራሱ በግል ሊሄድላቸው ለማይችለው፣ እነርሱም በአገልጋዮቹ አገልግሎት በኩል ቃላቶቹን ይሰሙ ዘንድ፣ የቤዛነት መልእክትን ለሙታን ሁሉ እንዲወስዱ ታውቋል።

፴፰ በዚህ ታላቅ የጻድቃን ስብሰባ ከተሰበሰቡት ታላቅ እና ሀያል ከሆኑት መካከል በዘመናት የሸመገለውና የሁሉም አባት፣ አባት አዳም ነበር፣

፴፱ እና የክብርም እናት ሔዋን፣ በዘመናት ውስጥ የኖሩት እና እውነት እና ህያው እግዚአብሔርን ካመለኩ ከብዙዎቹ ታማኝ ሴት ልጆቿ ጋር።

የመጀመሪያው ሰማዕት አቤል እና አባቱን አዳምን የሚመስለው ከሀይለኞቹ አንዱ ወንድሙ ሴትም በዚያ ነበሩ።

፵፩ ስለጎርፉ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ኖኅ፤ ታላቁ ሊቀ ካህን ሴም፤ የታማኞቹ አባት አብርሐምይስሀቅያዕቆብ፣ እና የእስራኤል ታላቅ ህግ ሰጪ ሙሴ

፵፪ እና በትንቢትም አዳኙ ልባቸው የተሰበረውን ይጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን ይናገር ዘንድ ተቀብቷል ያለው ኢሳይያስም በዚያ ነበሩ።

፵፫ በተጨማሪም፣ በራዕይ እንደ ህያው ነፍሳት ሙታን በትንሳኤ እንደገና ሲመጡ ወደፊትም በስጋ የሚሸፈኑትን የደረቁ አጥንቶች የተሞሉበት ታላቅ ሸለቆ ያየው ሕዝቅኤል

፵፬ ደግሞም የማይጠፋው ወይም ለሌሎች ሰዎች የማይሰጠው የእግዚአብሔር መንግስት በኋለኞቹ ቀናት መመስረትን ቀድሞ አይቶ እና ቀድሞ ነግሮ የነበረው ዳንኤልም

፵፭ ከሙሴ ጋር በክብር የመለወጥ ተራራ ላይ የነበረው ኢልያ

፵፮ እና ስለኤልያስ መምጣት የመሰከረው ነቢዩ ሚልክያስ—ስለዚህም ሞሮኒ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት ይመጣል በማለት ያወጀው ሞሮኒም—በዚያ ነበሩ።

፵፯ ነቢዩ ኤልያስ በልጆች ልብ ውስጥ የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳኖች ይተክላል፣

፵፰ ለሙታን ቤዛነት፣ እና ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር ለማስተሳሰር፣ መላው ምድር በምጽአቱ እንዳይረገሙ እና እንዳይጠፉ ዘንድ፣ በዘመን ፍጻሜ በጌታ ቤተመቅደሶች ውስጥ የሚደረገውን ታላቅ ስራ ቀድሞ ለማሳየት።

፵፱ እነዚህ ሁሉ እና ብዙ ተጨማሪዎች፣ እንዲሁም በኔፋውያን መካከል የኖሩት እና ስለእግዚአብሔር ልጅ መምጣት የመሰከሩት ነቢያት፣ በታላቁ ስብሰባ ውስጥ በመደባለቅ እና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ፣

ሙታን ሰውነታቸው ከመንፈሳቸው ለረዥም ጊዜ መለየቱን እንደ ባርነት ተመልክተውታልና።

፶፩ እነዚህንም ጌታ አስተማረ፣ እና ከትንሳኤው በኋላ ወደ አባቱ መንግስት በመግባት፣ በህያውነት እና በዘለአለም ህይወት አክሊል ይጫንላቸው ዘንድም እንዲመጡ ሀይልን ሰጣቸው፣

፶፪ እና ከዚህም በኋላ በጌታ ቃል እንደተገባው በአገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ፣ እና ለሚወዱትም ተጠብቀው የነበሩትን በረከቶች ሁሉ ተካፋይ እንዲሆኑ።

፶፫ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ፣ እና አባቴ ሀይረም ስሚዝ፣ ብሪገም ያንግ፣ ጆን ቴይለር፣ ዊልፈርድ ዉድረፍ፣ እና በዘመን ሙላት በታላቁ የኋለኛ ቀን ስራዎች መሰረትን ለመመስረት እንዲመጡ የጠበቁት ሌሎች ምርጥ መናፍስት፣

፶፬ በተጨማሪም ቤተመቅደሶችን ለመገንባት እና በእነዚያም ውስጥ ለሙታን ቤዛነት ስነስርዓቶችን ለማከናወን የጠበቁት ምርጥ መናፍስትም በመንፈስ አለም ውስጥ ነበሩ።

፶፭ እነርሱም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ውስጥ መሪዎች እንዲሆኑ የተመረጡት በተከበሩትና በታላቆቹ መካከል እንደነበሩም አየሁ።

፶፮ ከመወለዳቸውም በፊት ከብዙ ሌሎች ጋር የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በመንፈስ አለም ውስጥ የተቀበሉት እና በጌታ ጊዜ በወይን ስፍራው ለሰዎች የነፍስ ደህንነት እንዲያገለግሉ ለመምጣት ተዘጋጅተውም ነበር።

፶፯ የዚህ ዘመን ታማኝ ሽማግሌዎችም ከዚህ ህይወት ሲሄዱ የንስሀ መግባት እና በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መስዋዕት በኩል የቤዛነት ወንጌልን በጭለማ ውስጥ እና በሙታን መንፈሶች ታላቅ አለማት ውስጥ በኃጢአት ባርነት ላሉት በመስበክ አገልግሎታቸውን እንደሚቀጥሉ አየሁ።

፶፰ ንስሀ የገቡ ሙታንም የእግዚአብሔር ቤት ስርዓቶችን በማክበር ይድናሉ

፶፱ እና የተላለፉት ቅጣታቸውን ከተቀበሉና ለመንጻትም ከታጠቡ በኋላ፣ በስራዎቻቸው መሰረት ደመወዛቸውን ይቀበላሉ፣ የደህንነት ወራሾች ናቸውና።

እንደዚህም ነበር የሙታን ቤዛነት የተገለጠልኝ፣ እና እመሰክራለሁም፣ እና በጌታ እና አዳኝ በሆነው፣ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በረከት በኩል ይህ መዝገብ እውነት እንደሆነ አውቃለሁ፣ እንዲህም ይሁን። አሜን።