ክፍል ፹፰
በታህሳስ ፳፯ እና ፳፰፣ ፲፰፻፴፪፣ እና በጥር ፫፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ይህም በነቢዩ “‘የወይራ ቅጠል’…ከገነት ዛፍ የተቀጠፈች፣ ለእኛ የተሰጠ የጌታ የሰላም መልእክት” ተብሎ ተጠቁሞ ነበር። ይህም ራዕይ የተሰጠው ሊቀ ካህናት በጉባኤ “አንድ በአንድ እና በድምጽ ጌታ ለእኛ ስለፅዮን መገንባት ፍላጎቱን እንዲገልጽልን” ከጸለዩ በኋላ ነበር።
፩–፭፣ ታማኝ ቅዱሳን የዘለአለም ህይወት ተስፋ የሆነውን ያንን አፅናኝ ተቀበሉ፤ ፮–፲፫፣ ሁሉም ነገሮች በክርስቶስ ብርሀን ቁጥጥር ስር ያሉ እና የሚገዙ ናቸው፤ ፲፬–፲፮፣ ትንሳኤ የሚመጣው በቤዛነት በኩል ነው፤ ፲፯–፴፩፣ ለሰለስቲያል፣ ለተረስትሪያል፣ ወይም፤ ለቲለስቲያል ህግ ታዛዥ መሆን ሰዎችን ለእነዚህ መንግስታት እና ክብሮች ያዘጋጃል፤ ፴፪–፴፭፣ በኃጢአት የሚኖሩትም በመርከስ ይቀራሉ፣ ፴፮–፵፩፣ ሁሉም መንግስታት በህግ የሚገዙ ናቸው፤ ፵፪–፵፭፣ እግዚአብሔር ለሁሉም ነገሮች ህግ ሰጥቷል፤ ፵፮–፶፣ ሰው እግዚአብሔርንም እንኳ ይረዳዋል፤ ፶፩–፷፩፣ አገልጋዮቹን ወደ መስክ ልኮ እናም በየተራ ስለሚጎበኛቸው ሰው ምሳሌ፤ ፷፪–፸፫፣ ወደጌታ ቅረቡ፣ እናም ፊቱንም ታያላችሁ፤ ፸፬–፹፣ ራሳችሁን ቀድሱ እናም የመንግስትን ትምህርት እርስ በርስ ተማማሩ፤ ፹፩–፹፭፣ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው እያንዳንዱ ሰው ጎረቤቱን ሊያስጠነቅቅ ይገባዋል፤ ፹፮–፺፬፣ ምልክቶች፣ የፍጥረታት መናወጥ፣ እና መላዕክት የጌታን መምጫ መንገድ ያዘጋጃሉ፤ ፺፭–፻፪፣ መላዕክታዊ መለከቶች ሙታንን በየተራቸው እንዲነሱ ይጠሯቸዋል፤ ፻፫–፻፲፮፣ መላእክታዊ መለከቶች የወንጌሉን በዳግም መመለስ፣ የባቢሎንን መውደቅ፣ እና የታላቁን የእግዚአብሔር ጦርነት ያውጃሉ፤ ፻፲፯–፻፳፮፣ ትምህርትን ፈልጉ፣ የእግዚአብሔርን ቤት (ቤተመቅደስን) መስርቱ፣ እናም የልግስና ማሰሪያንም ልበሱ፤ ፻፳፯–፻፵፩፣ የነቢያት ትምህርት ቤት ስርዓት፣ እግሮችን የማጠብ ስርዓት በመጨመር፣ ተመድቧል።
፩ በእውነት፣ እናንተን በመመልከት ያለውን ፈቃዱን ለመቀበል ለተሰበሰባችሁት ጌታ እንዲህ ይላል፥
፪ እነሆ፣ ይህ ጌታን የሚያስደስት ነው፣ እናም መላእክትም በእናንተ ተደስተዋል፤ የጸሎታችሁ ምፅዋትም በፀባኦት ጌታ ጆሮዎች ውስጥ መጥተዋል፣ እናም በተቀደሱት ስሞች፣ እንዲሁም የሰለስቲያል አለም በሆኑት፣ መፅሀፍ ውስጥ ተመዝግበዋል።
፫ ስለዚህ፣ ለእናንተ፣ እንዲሁም ወደ እናንት ባልንጀሮቼ፣ በልባችሁ ውስጥ እንዲኖር፣ ሌላ አፅናኝ፣ እንዲሁም ቅዱስ የተስፋ መንፈስን እልክላችኋለሁ፤ ያም አፅናኝ፣ በዮሐንስ ምስክር ውስጥ እንደተመዘገበው፣ ለደቀመዛሙርቴ ቃል የገባሁላቸው ነው።
፬ ይህም አፅናኝ ለዘለአለም ህይወት፣ እንዲሁም የሰለስቲያል መንግስት ክብርን፣ እንደምሰጣችሁ የገባሁላችሁ ቃል ኪዳን ነው፤
፭ ይህም የበኩሩ ቤተክርስቲያን፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሆነ፣ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር ክብር ነው—
፮ እርሱም በሁሉም ነገሮች ውስጥና በሁሉም ነገሮች በኩል በመሆን የእውነት ብርሀን ይሆን ዘንድ፣ በዚህም ሁሉን ነገሮች እንዲረዳ ዘንድ፣ ወደላይ ያረገው፣ ደግሞም ከሁሉም ነገሮች በታች የወረደው ነው።
፯ ይህም እውነት ያበራል። ይህም የክርስቶስ ብርሀን ነው። እርሱም በጸሀይ ውስጥ፣ እናም የጸሀይ ብርሀን፣ እናም ያም የተሰራበት ሀይል ነው።
፰ እርሱም በጨረቃ ውስጥ፣ እናም የጨረቃ ብርሀን፣ እና ያም የተሰራበት ሀይል ነው፤
፱ የከዋክብትም ብርሀን፣ እናም እነዚህም የተሰሩበት ሀይል፤
፲ እናም ምድርንም፣ እናም ይህም ሀይል፣ እንዲሁም የቆማችሁበት ምድር ነው።
፲፩ እናም ብርሀን የሚሰጣችሁም፣ የሚበራው ብርሀንም፣ በእርሱ አይኖቻችሁን የሚያበራው በኩል ነው፣ ያ ብርሀንም የምትረዱበትን የሚያነሳሳው ነው፤
፲፪ ያም ከእግዚአብሔር ፊት ጠፈርን ለመሙላት የሚሄድ ብርሀን ነው—
፲፫ በሁሉም ነገሮች ውስጥ ነው፣ ለሁሉም ነገሮች ህይወት ይሰጣል፣ ሁሉም ነገሮች የሚገዙበት ህግ፣ እንዲሁም፣ በዘለአለም እቅፍ ውስጥ ያለው፣ በሁሉም ነገሮች መካከል ውስጥ ያለው፣ በዙፉኑ ላይ የሚቀመጠው የእግዚአብሔር ሀይል የሆነው ብርሀን ነው።
፲፬ አሁን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ለእናንተ በተደረገላችሁ ቤዛነት በኩል የሙታን ትንሳኤ ይመጣል።
፲፮ እናም የሙታን ትንሳኤ የነፍስ ቤዛነት ነው።
፲፯ እናም የነፍስ ቤዛነትም ሁሉንም ነገሮች ህይወት በሚሰጠው፣ በልቡ ድሀውና የዋሁ ምድርን ይወርሳሉ ተብሎ በታወጀበት በእርሱ በኩል ነው።
፲፰ ስለዚህ፣ ለሰለስቲያል ክብር ያዘጋጅ ዘንድ፣ ጽድቅ ካልሆነው ሁሉ መንጻት አለበት፤
፲፱ የተፈጠረበትን አላማ ካሟላ በኋላ፣ በክብር፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር አብም ፊት፣ ይነግሳል፤
፳ የሰለስቲያል መንግስት የሆኑት አካላት ለዘለአለም የራሳቸው ያደርጉት ዘንድ ነው፤ ለዚህም ምክንያት ተሰርቷል እና ተፈጥሯል፣ እናም ለዚህም ምክንያት ተቀድሷል።
፳፩ እናም በምሰጣችሁ ህግ፣ እንዲሁም በክርስቶስ ህግ፣ በኩል የማይቀደሱት፣ ሌላ መንግስትን፣ እንዲሁም የተረስትሪያል መንግስትን ወይም የቲለስቲያል መንግስትን፣ መውረስ አለባቸው።
፳፪ በሰለስቲያል መንግስት ህግ መፅናት የማይችለው በሰለስቲያል ክብር መፅናት አይችልምና።
፳፫ እና በተረስትሪያል መንግስት ህግ መፅናት የማይችለውም በተረስትሪያል ክብር መፅናት አይችልም።
፳፬ እና በቲለስቲያል መንግስት ህግ መፅናት የማይችለውም በቲለስቲያል ክብር መፅናት አይችልም፤ ስለዚህ ለመንግስት ክብር ብቁ አይደለም። ስለዚህ የክብር መንግስት ባልሆነ መንግስት ውስጥ መፅናት አለበት።
፳፭ ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ምድር በሰለስቲያል መንግስት ህግ ትጸናለች፣ የፍጥረቷን አላማ ታሟላለችና፣ እናም ህግጋትን አትተላለፍምና—
፳፮ ስለዚህ፣ ትቀደሳለች፤ አዎን፣ ምንም እንኳን የምትሞትም ቢሆን፣ ዳግም ህይወት ይሰጣታል፣ እናም ህይወት በተሰጠባት ሀይልም ትጸናለች፣ እናም ጻድቃንም ይወርሷታል።
፳፯ ምንም እንኳን ቢሞቱም፣ ዳግም እንደ መንፈሳዊ ሰውነት ይነሳሉ።
፳፰ ሰለስቲያል መንፈስ የሆኑትም ፍጥረታዊ ሰውነት የሆነውን አንድ አይነት ሰውነት ይቀበላሉ፤ እንዲሁም ሰውነታችሁን ትቀበላላችሁ፣ እናም ክብራችሁም ሰውነታችሁ ህይወት የተሰጠበት ያ ክብር ይሆናል።
፳፱ በሰለስቲያል ክብር ህይወት ከፊሉ የተሰጣችሁም፣ እንዲሁም ደግሞ ሙሉነትን፣ ትቀበላላችሁ።
፴ እናም በተረስትሪያል ክብር ክፍል ህይወት የተሰጣቸውም አንድ አይነት፣ እንዲሁም ሙሉነትን፣ ይቀበላሉ።
፴፩ እናም በቲለስቲያል ክብር ክፍል ህይወት የተሰጣቸውም አንድ አይነት፣ እንዲሁም ሙሉነትን፣ ይቀበላሉ።
፴፪ እናም የቀሩ ሰዎችም ህይወት ይሰጣቸዋል፤ ይህም ቢሆን፣ ሊያገኟቸው የሚችሉትን ለመቀበል ፈቃደኛ ስላልነበሩ፣ ለመቀበል ፈቃደኛ በሆኑት ለመደሰት ወደስፍራቸው ዳግም ይመለሳሉ።
፴፫ ለሰው ስጦታ ቢሰጠው እና ስጦታውን ባይቀበለው ምን ይጠቅመዋል? እነሆ፣ በተሰጠው አይደሰትም፣ ወይም በስጦታ ሰጪውም አይደሰትም።
፴፬ ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በህግ የሚመራው በህግ ይጠበቃል እና በዚህ ፍጹም ይሆናልም ይቀደሳልም።
፴፭ ህግን የሚሰብርና በህግ የማይጸናው፣ በራሱ ህግ ለመሆን የሚፈልገው፣ እና በኃጢአት ለመፅናት ፈቃደኛ የሆነው፣ እና ሁሉ በኃጢአት የሚጸናው ግን በህግ ወይም በምህረት፣ በፍትህ፣ ወይም በፍርድ ሊቀደስ አይችልም። ስለዚህ፣ ረክሰው መቅረት አለባቸው።
፴፮ ሁሉም መንግስታት የተሰጣቸው ህግ አላቸው፤
፴፯ እናም ብዙ መንግስታት አሉ፤ መንግስት የሌለበት ምንም ስፍራ የለም፤ እና፣ ታላቁ ወይም ታናሹ መንግስት፣ ስፍራ የሌለው ምንም መንግስት የለም።
፴፰ እናም ለእያንዳንዱም መንግስት ህግ ተሰጥቷል፤ እና ለእያንዳንዱም ህግ ልዩ ገደብና አካሄድ አላቸው።
፴፱ በእነዚህ አካሄዶች የማይጸኑትም ከጥፋት ነጻ አይሉም።
፵ የመረዳት ችሎታ ከመረዳት ችሎታ ጋር ይጣበቃል፤ ጥበብም ጥበብን ይቀበላል፤ እውነት እውነትን ያቅፋል፣ በጎነት በጎነትን ያፈቅራል፤ ብርሀን ከብርሀን ጋር ይጣበቃል፤ ምህረት በምህረት ላይ ርህራሄ አላት እና የራሷንም ታደርገዋለች፤ ፍትህ መንገዱን ይቀጥላል እናም የራሱንም ይወስዳል፤ ፍርድም በዙፋን ላይ በሚቀመጠውና ሁሉንም ነገሮች በሚመራውና በሚያከናውነው ፊት ይሄዳል።
፵፩ ሁሉንም ነገሮች ይረዳል፣ እና ሁሉም ነገሮች በፊቱ ናቸው፣ እና ሁሉም ነገሮች በዙሪያው ናቸው፤ እና በሁሉም ነገሮች ላይ፣ በሁሉም ነገሮች ውስጥ ነው፣ እና በሁሉም ነገሮች ከዳር እስከ ዳር ነው፤ እና ሁሉም ነገሮች በእርሱ፣ እና በእርሱ በኩል፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር፣ ለዘለአለም ናቸው።
፵፪ እና ዳግም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ለሁሉም ነገሮች በጊዜአቸው እና በወቅታቸው የሚሄዱበት ህግ ሰጥቷል፤
፵፫ እናም መንገዶቻቸውም፣ እንዲሁም ምድርን እና ፕላኔቶችን የሚያካትቱት የሰማያት እና የምድር መንገዶች፣ የተወሰኑ ናቸው።
፵፬ እናም በጊዜአቸው እና በወቅታቸውም፣ በደቂቃዎቻቸው፣ በሰአቶቻቸው፣ በቀናቶቻቸው፣ በሳምንቶቻቸው፣ በወራቶቻቸው፣ በአመቶቻቸው እርስ በራስ ብርሀን ይሰጣሉ—እነዚህም ሁሉ ለእግዚአብሔር አንድ አመት ናቸው፣ ነገር ግን ለሰው አይደሉም።
፵፭ ምድር በክንፎቿ ትሽከረከራለች፣ እናም ጸሀይ ብርሀኑን በቀን ይሰጣል፣ እና ጨረቃም ብርሀኗን በማታ ትሰጣለች፣ እና ከዋክብትም፣ በእግዚአብሔር ሀይል መካከል በክብር በክንፎቻቸው ሲሽከረከሩ፣ ብርሀናቸውን ይሰጣሉ።
፵፮ እንዲገባችሁ፣ እነዚህን መንግስታት ከምን ጋር ላመሳስል?
፵፯ እነሆ፣ እነዚህ ሁሉ መንግስታት ናቸው፣ እናም ማንኛውን ወይም ከእነዚህ ታናሾችን ያየ ማንም ሰው እግዚአብሔር በሞገሱ እና በክብሩ ሲሄድ አይቶታል።
፵፰ እላችኋለሁ፣ እርሱ አይቶታል፤ ይህም ቢሆን፣ የራሱ ወደ ሆኑት የመጣውንም አልተቀበሉትም።
፵፱ ብርሀንም በጭለማ ያበራል፣ እና በጨለማም ያሉት አይረዱትም፤ ይህም ቢሆን፣ በእርሱ ውስጥ እና በእርሱ ህይወት ተሰጥቷችሁ እግዚአብሔርን የምትረዱበት ቀን ይመጣል።
፶ ከዚያም እንዳያችሁኝ፣ እንደሆንኩኝ፣ እና በውስጣችሁ ያለሁት የእውነት ብርሀን እንደሆንኩኝ፣ እና እናንተም በእኔ ውስጥ እንዳላችሁ ታውቃላችሁ፤ አለበለዚያም ውጤታማ አትሆኑም።
፶፩ እነሆ፣ እነዚህን መንግስታት እርሻ ባለው ሰው አመሳስላቸዋለሁ፣ እናም አገልጋዮቹ እርሻውን ይቆፍሩ ዘንድ ወደ እርሻው ላካቸው።
፶፪ እና ለመጀመሪያው እንዲህ ይላል፥ ሂድ እና በእርሻው ስራ፣ እና በመጀመሪያው ሰዓት ወደአንተ እመጣለሁ፣ እና የፊቴ ደስታን ታያለህ።
፶፫ እና ለሁለተኛውም እንዲህ ይላል፥ አንተ ደግመህ ወደ እርሻው ሂድ፣ እና በሁለተኛው ሰዓት በፊቴ ደስታ እጎበኝሀለሁ።
፶፬ እና ደግሞም ለሶስተኛውም አለ፥ እጎበኝሀለሁ።
፶፭ እና ለአራተኛውም፣ እና ቀጥሎም ለአስራ ሁለቱ።
፶፮ በመጀመሪያው ሰዓት የእርሻው ጌታ ወደ መጀመሪያው ሄደ፣ እና በዚያ ሰዓት ሁሉ ከእርሱ ጋር ቆየ፣ እና እርሱም በጌታው ፊት ብርሀን ተደሰተ።
፶፯ እና ከዚያም ሁለተኛውን፣ እና ሶስተኛውን፣ እና አራተኛውን፣ እና እስከ አስራሁለተኛው ድረስ ደግሞ ለመጎብኘት ከመጀመሪያው ተለይቶ ሄደ።
፶፰ እንደዚሁ ሁሉም፣ እያንዳንዱ በሰዓቱ፣ እና በጊዜው፣ እና በወቅቱ፣ የጌታቸውን ፊት ብርሀን ተቀበሉ—
፶፱ ከመጀመሪያው ጀምሮ፣ እና እስከመጨረሻው በመቀጠል፣ እና ከመጨረሻው እስከመጀመሪያው፣ እና ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው እንዲህ ተቀበሉ፤
፷ ጌታው በእርሱ እና እርሱም በጌታው፣ ይከብር ዘንድ፣ ሁሉም ይከብሩ ዘንድ፣ እያንዳንዱም ሰው ሰዓቱ እስኪያልቅ ድረስ፣ እንዲሁም ጌታው እንዳዘዘው እንዲሁ ተቀበለ።
፷፩ ስለዚህ፣ በዚህ ምሳሌ እነዚህን መንግስታት፣ እና የሚኖሩባቸውን፣ እንዲሁም በሰአቱ፣ እና በጊዜው፣ እና በወቅቱ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር ባወጀው ያሉትን እያንዳንዱ መንግስት እመስላለሁ።
፷፪ እና ዳግም፣ ባልንጀሮቼ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በቅርብ እያለሁ እንድትጠሩኝ ዘንድ፣ ከምሰጣችሁ ከዚህ ትእዛዝ ጋር፣ እነዚህን አባባሎች በልባችሁ እንድታሰላስሏቸው እተውላችኋለሁ—
፷፫ ወደ እኔ ቅረቡ እና እኔም ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ ተግታችሁም ፈልጉኝ እናም ታገኙኝማላችሁ፤ ለምኑ፣ እናም ይሰጣችኋል፤ አንኳኩ፣ ይከፈትላችሁማል።
፷፬ ለእናንተ አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም ነገር በስሜ አብን ብትለምኑ፣ ይሰጣችኋል።
፷፭ እናም ለእናንተ አስፈላጊ ያልሆነውን ብትጠይቁ፣ ወደ ኩነኔም ይቀየርባችኋል።
፷፮ እነሆ፣ የምትሰሙት በምድረበዳ እንደሚጮኽ ሰው ድምፅ ነው—በምድረበዳ፣ ምክንያቱም ልታዩት አትችሉምና—ድምጼ፣ ምክንያቱም ድምጼ መንፈስ ነውና፤ መንፈሴም እውነት ነው፤ እውነትም ይጸናልና መጨረሻም የለውም፤ እና በእናንተ ቢሆንም ይበዛል።
፷፯ እና ወደ ክብሬ ዐይኖቻችሁ ቢያተኩሩ፣ ሰውነታችሁ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፣ እና በእናንተም ምንም ጭለማ አይኖርም፤ እና ብሩህ የሆነ ሰውነትም ሁሉንም ነገሮች ይረዳል።
፷፰ ስለዚህ፣ አዕምሮዎቻችሁ ለእግዚአብሔር የቀኑ እንዲሆኑ ራሳችሁን ቀድሱ፣ እናም እርሱን የምታዩበት ቀን ይመጣል፤ ፊቱን ለእናንተ ይገልጣልና፣ እና ይህም በራሱ ጊዜና፣ በራሱ መንገድ፣ እናም እንደ ፈቃዱ ይሆናል።
፷፱ የሰጠኋችሁን ታላቅ እና የመጨረሻ ቃል ኪዳን አስታውሱ፤ ከንቱ ሀሳቦቻችሁንና ከልክ በላይ የሆኑ ሳቆችን ከእናንተ አስወግዱ።
፸ ቆዩ፣ በዚህም ስፍራ ቆዩ፣ እና የክብር ስብሰባን፣ እንዲሁም በእዚህ በመጨረሻው መንግስት የመጀመሪያ አገልጋዮች የሆኑትን፣ ጥሩ።
፸፩ እናም ያስጠነቀቋቸውም በጉዞአቸው ጌታን ይጥሩ፣ እና ለጥቂት ወቅትም የተቀበሉትን ማስጠንቀቂያ በልቦቻቸው ያሰላስሉ።
፸፪ እነሆ፣ እናም አስተውሉ፣ መንጋዎቻችሁን እንከባከባለሁ፣ እና ሽማግሌዎችን አስነሳለሁ እና ወደ እነርሱም እልካለሁ።
፸፫ እነሆ፣ ስራዬን በራሱ ጊዜ አፈጥናለሁ።
፸፬ እናም የዚህ የመጨረሻ መንግስት የመጀመሪያ አገልጋዮች ለሆናችሁ፣ አብራችሁ እንድትሰበሰቡ፣ እና ራሳችሁን እንድታደራጁ፣ እና ራሳችሁን እንድታዘጋጁ፣ እና ራሳችሁን ትቀድሱ ዘንድ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ አዎን፣ አነጻችሁም ዘንድ ልባችሁን አንጹ፣ እጆቻችሁን እና እግሮቻችሁንም በፊቴ የጸዱ ይሁኑ፤
፸፭ ከዚህ ክፉ ትውልድ ደም ንጹህ መሆናችሁን ወደ አባታችሁ፣ አምላካችሁና፣ አምላኬ፣ እመሰክር ዘንድ፤ እንደ ፈቃዴም የገባሁላችሁ ቃል ኪዳን፣ ይህን ታላቅ እና የመጨረሻ ቃል ኪዳን፣ ላሟላ እችል ዘንድ ነው።
፸፮ ደግሞም፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በጸሎት እና በጾም ትበረቱም ዘንድ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።
፸፯ እናም የመንግስቱን ትምህርት እርስ በርስ ትማማሩም ዘንድ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።
፸፰ በትጋት አስተምሩ እናም፣ ጸጋዬ ከእናንተ ጋር ይሆናል፣ ይህም በፅንሰ ሀሳብ፣ በመሰረታዊ መርሆች፣ በትምህርት፣ በወንጌሉ ህግ፣ ከእግዚአብሔር መንግስት ጋር ግኑኝነት ባላቸው ሁሉም ነገሮች፣ ለእውቀታችሁ አስፈላጊ የሆኑትን ፈጽማችሁ እንድትማሩ ዘንድ፤
፸፱ በሰማይና ምድር፣ እናም ከምድር በታች፣ ስላሉትም ነገሮች፤ ስለነበሩት ነገሮች፣ ስለአሉ ነገሮች፣ እና በቅርብም ስለሚሆኑት ነገሮች፤ በቤት ስላሉም ነገሮች፣ በሌሎች ሀገሮች ስላሉትም ነገሮች፤ ስለህዝብ ጦርነቶች እና አወዛጋቢ ጉዳዮች፣ እና በምድር ላይ ስላሉት ፍርዶች፤ እና የሀገራት እና የመንግስታትም እውቀቶች በፍጹም እንድትማሩ ዘንድ፣ ጸጋዬ ከእናንተ ጋር ይሆናል—
፹ በተጠራችሁበት ጥሪ፣ እና በልዩ ሀላፊነት በሰጠኋችሁ ተልዕኮ፣ ጥሪዎቻችሁን እንድታጎሉ በምልካችሁ ጊዜ በሁሉም ነገሮች ትዘጋጁ ዘንድ ጸጋዬ ከእናንተ ጋር ይሆናል።
፹፩ እነሆ፣ የላኳችሁ እንድትመሰክሩ እና ሰዎችን እንድታስጠነቅቁ ነው፣ እናም የተጠነቀቀው ሰው ባልንጀራውን ማስጠንቀቁ አስፈላጊ ነው።
፹፪ ስለዚህ፣ ምክንያትም አይኖራቸውም፣ እና ኃጢአቶቻቸውም በራሳቸው ላይ ናቸው።
፹፫ ከጊዜው ቀድሞ የሚፈልገኝም ያገኘኛል፣ እና አይተውም።
፹፬ ስለዚህ ለመጨረሻ ጊዜ በአህዛብ መካከል በመሄድ በአገልግሎታችሁ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ፤ የጌታም አንደበት የጠራቸውን ሁሉ ለማምጣት፤ ህግን ለማሰር እና ምስክርንም ለማተም እና ከሚመጣውም የፍርድ ሰአት ቅዱሳንን ታዘጋጁ ዘንድ ቆዩ እናም ተግታችሁም ስሩ።
፹፭ ነፍሳቸውም በዚህም ሆነ በሚመጣው አለም ክፉዎችን የሚጠብቀውን፣ የርኩሰጥ ጥፋት የሆነውን፣ የእግዚአብሔር ቁጣ ያመልጥ ዘንድ ቅዱሳንን ታዘጋጁ ዘንድ ቆዩ እናም ተግታችሁም ስሩ። እውነት እላችኋለሁ የጌታ አንደበት እስኪጠራቸው ድረስ የመጀመሪያ ያልሆኑት ሽማግሌዎች በወይኑ ስፍራ መስራታቸውን ይቀጥሉ፤ ሰአታቸው ገና አልደረሰምና፤ ልብሶቻቸውም ከዚህ ትውልድ ደም የነጹ አይደሉም።
፹፮ ነጻ ሆናችሁ በተፈጠራችሁበትም አርነት ጸንታችሁ ቁሙ፤ በኃጢአትም ራሳችሁን አትጥመዱ፣ ነገር ግን፣ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ፣ እጆቻችሁን እንዲጸዱ አድርጉ።
፹፯ ለብዙ ቀናት ሳይቆይ እና ምድርም እንደሰካራም ሰው ትፍገመገማለች እና ወዲህና ወዲያ ትናወጣለች፣ እና ጸሀይም ፊቷን ትሰውራለች፣ ብርሀኗንም ትከለክላለች፤ እና ጨረቃም በደም ትርሳለች፤ እና ከዋክብትም እጅግ ይቆጣሉ፣ እናም የበለስ ፍሬ ከበለስ እንደሚወድቅም ራሳቸውን ይጥላሉ።
፹፰ እና ከምስክርነታችሁ በኋላ በህዝብ ላይ ንዴት እና ቁጣ ይመጣል።
፹፱ ከምስክርነታችሁ በኋላ፣ በመካከሏ ሁከት የሚያመጣ የምድር መናወጥ ምስክርነት ይመጣል፣ እና ሰዎችም ወደ ምድር ይወድቃሉ እናም ለመነሳትም ይሳናቸዋል።
፺ እና ደግሞም የነጎድጓድ፣ እና የመብረቅ ድምፅ፣ እና የማእበል ድምፅ፣ እና ከገደባቸው በላይ ራሳቸውን በሚወረውሩ የባህር ማዕበል ድምፅ ምስክርነት ይመጣል።
፺፩ እና ሁሉም ነገሮች በሁከት ውስጥ ይሆናሉ፣ እና በእርግጥም፣ የሰዎች ልብ በፍርሀት ይደክማል፤ ፍርሀት በሁሉም ሰዎች ላይ ይመጣልና።
፺፪ እናም፣ ተዘጋጁ፣ ተዘጋጁ፣ በምድር የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔር ፍርድ መጥቷልና። እነሆ፣ እና አስተውሉ፣ ሙሽራው መጥቷል፤ ከእርሱ ጋር ለመገናኘትም ውጡ በማለት፣ በከፍተኛ ድምፅ በመጮህ፣ የእግዚአብሔርን መለከት በመንፋት፣ መላዕክትም በሰማይ መካከል ይበራሉ።
፺፫ እና ወዲያውም በሰማይ ታላቅ ምልክት ይታያል፣ እናም ሁሉም ሰዎች አብረው ያዩታል።
፺፬ እና ሌላም መልአክ መለከቱን እንዲህ በማለት ይነፋል፥ ህዝብን ሁሉ የዝሙቷን ቁጣ ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገችው፣ የእግዚአብሔን ቅዱሳን የምታሳድድ፣ ደማቸውን የምታፈስ—በብዙ ውሀዎች እና በባህር ደሴቶች ላይ የተቀመጠችው—ያቺ ታላቅ ቤተክርስቲያን፣ የርኩሰት እናት፣ እነሆ፣ የምድር እንክርዳድ እርሷ ነች፤ አንድ ላይ ታስራለች፤ እስሯም ተጠናክሯል፣ እና ማንም ሰው ሊፈታው አይችልም፤ ስለዚህ፣ ለመንደድ ተዘጋጅታለች። እና መለከቱም ረጅም እና ጉልህ ይሆናል፣ እና ሁሉም ህዝብ ይሰሙታል።
፺፭ እና በሰማይም ለግማሽ ሰአት ያህል ጸጥታ ይሆናል፤ እና ወዲያውም፣ መጽሐፍ ጥቅልል ከተጠቀለለ በኋላ እንደሚዘረጋ፣ የሰማይ መጋረጃዎች ይዘረጋሉ፣ እናም የጌታ ፊትም ይገለጣል፤
፺፮ እና በህይወት በምድር ላይ ያሉት ቅዱሳን በቅፅበት ይለወጣሉ እና እርሱን ያገኑት ዘንድም ይነጠቃሉ።
፺፯ እና በየመቃብራቸው ያንቀላፉትም ይነሳሉ፣ መቃብሮቻቸውም ይከፈታሉና፤ እና እነርሱ ደግመውም በሰማይ አምድ መካከል እርሱን ለመቀበል ይነጠቃሉ—
፺፰ መጀመሪያ ከእርሱ ጋር የሚወርዱት፣ እና በምድርና በመቃብራቸው ያሉት፣ እርሱን ለመቀበል የተነጠቁት፣ እነርሱም የክርስቶስ፣ የመጀመሪያ ፍሬዎች፣ ናቸው፤ እና ይህም ሁሉ የሚሆነው የእግዚአብሔር መልአክ መለከት ድምፅ ሲሰማ ነው።
፺፱ ከዚህ በኋላም ሌላ መልአክ፣ ሁለተኛው መለከት፣ ያሰማል፤ ከዚያም፣ ወንጌልን ለመቀበልና እንደሰዎች በሥጋ ይፈረድባቸው ዘንድ፣ በወህኒ ለእነርሱ የተዘጋጀውን ድርሻቸውን የተቀበሉት፣ በመምጫው ጊዜ የክርስቶስ የሆኑት ቤዛነትም ይመጣል።
፻ ደግሞም፣ ሶስተኛው መለከት የሆነው ሌላ መለከት ይነፋል፤ ከዚያም የሚፈረድባቸውና በኩነኔ የሚገኙት ሰዎች ነፍሳት ይመጣሉ፤
፻፩ እነዚህም የቀሩት ሙታን ናቸው፤ እና ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፣ ያም እስከምድር ፍጻሜም ድረስ፣ በሕይወት አይኖሩም።
፻፪ እና አራተኛው መለከት የሆነው ሌላ መለከትም እንዲህ በማለት ይነፋል፥ እስከታላቅ እና መጨረሻው ዘመን፣ እንዲሁም እስከፍጻሜው፣ ድረስ ከሚቀሩት መካከል ቆሽሸው የሚቀሩ አሉ።
፻፫ እና አምስተኛው መለከት የሆነው፣ ዘለአለማዊውን ወንጌል በሰማይ መካከል በመብረር ለሀገር ለነገድ ለቋንቋ ለህዝብ የሚሰብከው አምስተኛው መልአክ፣ ሌላውን መለከት ይነፋል፤
፻፬ ይህም፣ ለህዝብ ሁሉ በማለት፣ የመለከቱ ድምፅ ይሆናል፣ በሰማይና በምድር፣ እና ከምድር በታች ላሉት—ሁሉም ጆሮዎች ይሰሙታልና፣ እና የመለከቱንም ድምፅ እንዲህ ሲል ሲሰሙም፣ ጉልበት ሁሉ ይንበረከካል ምላስም ሁሉ ይናዘዛል፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ እና በዙፋኑ ላይ ከዘለአለም እስከ ዘለአለም ለሚቀመጠው ክብሩን ስጡ፤ የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና።
፻፭ እና ደግሞም፣ ስድስተኛው መልአክ የሆነው ሌላ መልአክም መለከቱን እንዲህ በማለት ይነፋል፥ ህዝብን ሁሉ የዝሙቷን ቁጣ ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገችው ወድቃለች፤ ወድቃለች፣ ወድቃለች!
፻፮ እና ዳግም፣ ሰባተኛው መልአክ የሆነው ሌላ መልአክ መለከቱን እንዲህ በማለት ይነፋል፥ ተፈፅሟል፤ ተፈፅሟል! የእግዚአብሔር በግ አሸንፎታል እናም መጥመቂያውን፣ እንዲሁም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያን፣ ብቻውን ረግጦታል።
፻፯ ከዚያም መላእክቱ የሀይሉን የክብር አክሊል ይደፋሉ፣ እና ቅዱሳንም በክብሩ ይሞላሉ፣ እና ውርሳቸውን ይቀበላሉ እና ከእርሱም ጋር እኩል ይደረጋሉ።
፻፰ ከዚያም የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ዳግም በሚኖሩት ጆሮዎች ላይ ያሰማል፣ እና የሰዎችን የሚስጥር ስራዎችና በመጀመሪያው ሺህ አመታት የእግዚአብሔርን ታላቅ ስራዎች ይገልጣል።
፻፱ ከዚያም ሁለተኛው መልአክ መለከቱን ይነፋል፣ እና የሰዎችን የሚስጥር ስራዎች፣ እና የልባቸውን ሀሳብና ስሜታቸውን፣ እና በሁለተኛው ሺህ አመታት የእግዚአብሔርን ታላቅ ስራዎች ይገልጣል—
፻፲ እናም ሰባተኛው መልአክ መለከቱን እስከሚነፋ ድረስ ይቀጥላል፤ እና በምድር ላይ እና በባህር ላይ ይቆማል፣ እና ዘመንም እንደሚፈጸም በዙፋኑ ላይ በሚቀመጠው ስም ይምላል፤ እና የቀደመውንም እባብ፣ ዲያብሎስ የሚባለው፣ ሰይጣንም ይያዛል፣ እና ለአንድ ሺህ ለሚሆን ዘመንም አይፈታም።
፻፲፩ ከዚያም ሰራዊቱን ለመሰብሰብ ይችል ዘንድ ለትንሽ ዘመን ይለቀቃል።
፻፲፪ እና ሰባተኛው መልአክ ሚካኤል፣ እንዲሁም የመላእክት አለቃው፣ ሰራዊቱን፣ እንዲሁም የሰማይ ሰራዊትን፣ ይሰበስባል።
፻፲፫ እና ዲያብሎስም ሰራዊቱን ይሰበስባል፤ እንዲሁም የሲኦል ሰራዊትን፣ እና ከሚካኤልና ከሰራዊቱ ጋር ለመዋጋት ይመጣል።
፻፲፬ ከዚያም የታላቁ እግዚአብሔር ጦርነት ይመጣል፤ እና በቅዱሳን ላይ ከዚህ በኋላ ሀይል እንዳይኖራቸው፣ ዲያብሎስና ሰራዊቱ ወደራሳቸው ስፍራም ይጣላሉ።
፻፲፭ ሚካኤል ጦርነታቸውን ይዋጋላቸዋልና፣ እና በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን፣ እንዲሁም የበጉን፣ ዙፋን የሚፈልገውን ያሸንፋል።
፻፲፮ ይህም የእግዚአብሔርና የተቀደሱት ክብር ነው፤ እና ከዚህም በኋላ ሞትን አይቀምሱም።
፻፲፯ ስለዚህ፣ ባልንጀሮቼ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እንዳዘዝኳችሁ የክብር ስብሰባችሁን ጥሩ።
፻፲፰ እና ሁሉም እምነት ስለሌላቸው፣ ተግታችሁ ፈልጉ እና እርስ በርሳችሁም የጥበብ ቃላትን ተማማሩ፤ አዎን፣ ከተመረጡት መጽሀፍትም የጥበብን ቃላት ፈልጉ፤ እውቀትን፣ እንዲሁም በጥናትና ደግሞም በእምነት፣ እሹ።
፻፲፱ ራሳችሁን አደራጁ፤ አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ አዘጋጁ፤ ቤትን፣ እንዲሁም የጸሎትን ቤት፣ የጾምን ቤት፣ የእምነትን ቤት፣ የእውቀትን ቤት፣ የክብርን ቤት፣ የስርዓትን ቤት፣ የእግዚአብሔርን ቤት መስርቱ፤
፻፳ በእዚህም መግባታችሁ በጌታ ስም ይሆን ዘንድ፤ መውጣታችሁም በጌታ ስም ይሆን ዘንድ፤ ሰላምታችሁም፣ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጆቻችሁን በማንሳት፣ በጌታ ስም ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት መስርቱ።
፻፳፩ ስለዚህ፣ ጥቅም የሌለውን ንግግራችሁን ሁሉ፣ ሳቆችን ሁሉ፣ ከፍተኛ ፍላጎታችሁን ሁሉ፣ ኩራታችሁን እና ተራ አስተሳሰባችሁን ሁሉ፣ እና ክፉ ድርጊታችሁን ሁሉ አቁሙ።
፻፳፪ ከመካከላችሁም መምህር መድቡ፣ እና ሁሉም ታናጋሪ እንዲሆኑ አታድርጉ፤ ነገር ግን፣ ሁሉም ሲናገሩ ሁሉም ይታነጹ ዘንድ፣ እና እያንዳንዱም ሰው እኩል ባለመብት ይሆን ዘንድ፣ አንድ በአንድ በተራ እንዲናገር አድርጉ እና ሁሉም የሚነገረውን እንዲሰሙ አድርጉ።
፻፳፫ እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን አረጋግጡ፤ ትምክህተኞች አትሁኑ፤ በወንጌሉ አስፈላጊ እንደሆነም እርስ በርስ መካፈልን ተማሩ።
፻፳፬ ስራ ፈት መሆንን አቁሙ፤ እርኩስ መሆንንም አቁሙ፤ እርስ በራስ ስህተት መፈለግን አቁሙ፤ አስፈላጊ ከሆነው በላይ መተኛትንም አቁሙ፤ እንዳትደክሙ፣ ወደመኝታችሁ በጊዜ ሂዱ፤ ሰውነቶቻችሁ እና አዕምሮዎቻችሁ ይነቃቁ ዘንድም በማለዳ ተነሱ።
፻፳፭ እና ከሁሉም በላይ፣ የፍጹምነትና የሰላም ማሰሪያ የሆነውን ልግስና፣ እንደ ካባ፣ ልበሱት።
፻፳፮ እስከምመጣም ድረስ ሳትታክቱ ዘንድ፣ ዘወትር ጸልዩ። እነሆ እናም አስተውሉ፣ በቶሎ እመጣለሁ፣ እናም እናንተንም ወደራሴ እወስዳችኋለሁ። አሜን።
፻፳፯ ደግሞም፣ ለነብያቱ ትምህርት ቤት አመራር፣ እንዲሁም ለቤተክርስቲያን ሹማምንቶች ሁሉ፣ ወይም በሌላ ቃል፣ ከሊቀ ካህናት ጀምሮ እስከ ዲያቆን ድረስ በቤተክርስቲያኑ እንዲያገለግሉ ለተጠሩት ተዘጋጅቶ፣ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ እንዲማሩበት የተመሰረተውን ቤት ስርዓት በሚመለከት—
፻፳፰ እናም ይህም የትምህርት ቤቱ አመራር ቤት ስርዓት ይሆናል፥ ፕሬዘደንት ወይም መምህር እንዲሆን የተሾመው በሚዘጋጅለት ቤት ውስጥ በስፍራው ቆሞ ይገኝ።
፻፳፱ ስለዚህ፣ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በጎላ ንግግር ሳይሆን፣ በቤቱ ውስጥ ያሉት ተሰብሳቢዎች ቃላቶቹን በጥንቃቄና በግልፅ በሚሰሙበት ስፍራ መጀመሪያ ይሁን።
፻፴ እና ወደ እግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሲመጣም፣ በቤቱ ውስጥ የመጀመሪያ መሆን ይገባዋልና—እነሆ፣ ይህም ድንቅ ነው፣ ምሳሌም ይሆን ዘንድ—
፻፴፩ የዘለአለማዊ ቃል ኪዳን ምልክት ወይም ማስታወሻም ይሆን ዘንድ፣ በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት በመንበርከክ እራሱን ያቅርብ።
፻፴፪ እናም ከእርሱ በኋላ ማንም ሲገባ፣ መምህሩ ይነሳ፣ እና ወደሰማይ በተዘረጉ እጆች፣ አዎን፣ እንዲሁም በቀጥታ፣ ወንድሙን ወይም ወንድሞችን በእነዚህ ቃላት ሰላም ይበላቸው፥
፻፴፫ እናንት ወንድም ወይም ወንድሞች ናችሁ? በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ በምልክት ወይም በዘለአለማዊ ቃል ኪዳን ማስታወሻ ሰላም እላችኋለሁ፣ በዚህም ቃል ኪዳን፣ በማይለወጥ፣ በማይነቃነቅ፣ እና በማይቀየር ቁርጥ ውሳኔ፣ በእግዚአብሔር ጸጋ በፍቅር እስር ውስጥ፣ በእግዚአብሔር ትእዛዛት ሁሉ ያለእንከን፣ በምስጋና መስጠት፣ ከዘለአለም እስከዘለአለም ጓደኛችሁና ወንድማችሁ ለመሆን ወደ ማህበርተኛነት እቀበላችኋለሁ። አሜን።
፻፴፬ እናም ለዚህ ሰላምታ ብቁ ሆኖ የማይገኘውም ከመካከላችሁ ምንም ስፍራ አይኑረው፤ ቤቴ በእርሱ እንዲረከስ አትፈቅዱምና።
፻፴፭ እና የሚገባውና በፊቴ ታማኝ የሚሆነው፣ እና ወንድም የሆነው፣ ወይም ወንድሞችም ከሆኑ፣ ወደሰማይ በተዘረጉ እጆች፣ በአንድ አይነት ጸሎት እና ቃል ኪዳን፣ ወይም በአንድ አይነት ምልክት አሜን በማለት ለፕሬዘደንት ወይም ለመምህሩ ሰላምታ ይሰጣሉ።
፻፴፮ እነሆ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ይህም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ፣ በነቢያትም ትምህርት ቤት ውስጥ፣ እርስ በርስ ሰላምታ የምትሰጣጡበት ምሳሌ ነው።
፻፴፯ እናም መሸሸጊያ፣ ለምትታነጹበት የመንፈስ ቅዱስ ድንኳን ይሆን ዘንድ፣ በጌታ ቤት፣ እንዲሁም በነቢያት ትምህርት ቤት ውስጥ፣ መንፈስ በሚናገረው በምታደርጉት ሁሉ ጸሎት እና ምስጋና በመስጠት እንድታደርጉ ተጠርታችኋል።
፻፴፰ እና ከዚህ ትውልድ ደም ንጹህ ያልሆነን በመካከላችሁ ማንንም ወደ እዚህ ትምህርት ቤት አትቀበሉ።
፻፴፱ እና እርሱም እግርን ማጠብ በሆነ ስርዓት ተቀበሉት፣ ለዚህም ምክንያት ነበር የእግር ማጠብ ስነስርዓት የተመሰረተው።
፻፵ ደግሞም፣ የእግር ማጠብ ስርዓት የሚከናወነው በፕሬዘደንቱ፣ ወይም በቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች አመራር ነው።
፻፵፩ ይህም የሚጀምረው በጸሎት ነው፤ እና ዳቦው እና ወይኑ ከተሰጠ በኋላ፣ እኔን በሚመለከት በዮሐንስ ምስክር ምዕራፍ አስራ ሶስት ውስጥ በምስክርነት በሰጠው ምሳሌ ራሱን ያልብስ። አሜን።